ክርስትና በኢትዮጵያ
"ኢትዮጵያ እጆቿን ወደ እግዚአብሔር ትዘረጋለች" መዝ፤ 67፡ 31 መግቢያ ኢትዮጵያ ክርስትናን በዘመነ ሐዋርያት በቀዳሚነት ከተቀበሉ እጅግ በጣም ጥቂት አገሮች አንዷ ናት። ክርስትና ወደ ኢትዮጵያ ከመግባቱ ቀደም ብሎየአይሁድ ሃይማኖት በስፋት ሲሰበክ የነበረ ሲሆን የቤተመንግሥቱና የሕዝቡ ብሔራዊ ሃይማኖትም ሆኖ ብዙ ጊዜ ቆይቷል። ስለሆነም ኢትዮጵያሁለቱንም የመጽሐፍ ቅዱስ ሃይማኖቶች (የኦሪትንና የክርስትናን ሃይማኖት) በመቀበልና በማስፋፋት ከሌሎች አገሮች ልዩ ናት። 1. ቅድመ ክርስትና ስለ ኢትዮጵያውያን የአምልኮ ሥርዓት (ሃይማኖት) የሃይማኖትና የታሪክ ጥናት ባለሙያዎች የተለያየ አስተያየት የሚሰጡ ቢሆንም በአንድ አምላክ ማመን (Monotheism) ከጥንት ጀምሮ እንደነበረና ቢያንስ የአይሁድ ሃይማኖት (Judaism) ከ1000 ዓመት በላይ፣ ክርስትና ለ1630 ዓመታት ያህል ብሔራዊ ሃይማኖት ሆነው እንደቆዩ ይስማማሉ። እንደ ተክለ ጻድቅ መኩሪያ ያሉ የታሪክ ጸሐፊዎች የኢትዮጵያውያን ሃይማኖት እንደ ሌሎች ጥንታውያን ሕዝቦች ሁሉ አምልኮ ጣዖት እንደነበረ ይገልጻሉ። ክብረ ነገሥት የተባለው ጥንታዊ የታሪክ መጽሐፍም በንግሥተ ሳባ ዘመነ መንግሥት በአንድ አምላክ (እግዚአብሔር) ማመን በይፋ እስከ ተጀመረበት ጊዜ ድረስ በአክሱም አካባቢ አርዌ የሚባል ዘንዶ ይመለክ እንደነበር ይገልጣል። በአንጻሩ ግን በኢትዮጵያ ጣዖት በይፋ ተመልኮ እንደማያውቅ የሚያስረዱ ምሁራን አሉ። በንግሥተ ሳባ ዘመን የኦሪት እምነት ከመግባቱ በፊትም ቢሆን ኢትዮጵያውያን አንድ አምላክ እግዚአብሔርን ያምኑ ነበር። ይህም የሆነበትን ምክንያት ሲገልጹ ከኖኅ ልጆች (ሴም፣ ካም፣ ያፌት) መካከል ካም ወደ አፍሪቃ መጥቶ ስለኖረ እርሱም ልጆቹም አንድ አምላክን ማመን እንዳስፋፉ ያብራራሉ። ንግሥተ ሳባም ወደ ሰሎሞን በሄደችበት ወቅት “ አንተን የወደደ፣በእስራኤልም ዙፋን ያስቀመጠህ እግዚአብሔር የተባረከ ይሁን፤…”(1ነገ፤ 10፡9) ብላ እግዚአብሔርን ያመሰገነችው ከጥንት ከትውልደ ካም ( ኩሽ) ሲያያዝ በመጣው አምልኮተ እግዚአብሔር መሆኑን መገንዘብ ያስፈልጋል። በአጠቃላይ ኢትዮጵያውያን በሦስቱም ሕግጋት (በሕገ-ልቡና፣ በሕገ-ኦሪተ፣ በሕገ-ወንጌል) አንድ አምላክ እግዚአብሔርን በማመን እንደኖሩ የቤተክርስቲያን ታሪክ ሊቃውንት ያብራራሉ። በአጠቃላይ ቀደም ባለው ጊዜ በኢትዮጵያ ጣዖት ይመለክ ነበር የሚሉ ቢኖሩ እንኳን ከክርስቶስ ልደት በፊት ከ1000 ዓመት ጀምሮ የኢትዮጵያውያን ብሔራዊ ሃይማኖት በአንድ አምላክ ማመን (Monotheism) መሆኑ የማያከራክር ሃቅ ነው። ይሁዲነት (Judaism) እና ክርስትና (Christianity) አንድ አምላክን በማመን (Monotheism) ብቻ ሳይሆን አብርሃምን በአባትነት፣ የአብርሃምን አምላክ እግዚአብሔርን በፈጣሪነት በመቀበል ይተባበራሉ። ስለዚህም በንጽጽራዊ የሃይማኖቶች ጥናት (Comparative Study of Major Religions) አከፋፈል አብርሃማዊ ሃይማኖቶች (Abrahamic Religions) ተብለው ከሚጠሩት ጋር ይቆጠራሉ። እነዚህ ሃይማኖቶች የተመሠረቱት በመካከለኛው ምሥራቅ በመሆኑ የመካከለኛው ምሥራቅ ሃይማኖቶች (Middle-East Religions) በመባልም ይታወቃሉ። የኢትዮጵያ ታሪክ ምንጭ ከሆኑት ጥቂት ጥንታውያን የታሪክ መጻሕፍት መካከል ቀዳሚውን ሥፍራ የሚይዘው፣ በ13ኛው መቶ ክፍለ ዘመን በአክሱም የተጻፈው ክብረ ነገሥት የተሰኘው የታሪክ መጽሐፍ ከመጽሐፍ ቅዱስ በመጽሐፈ ነገሥት እና መጽሐፈ ዜና መዋዕል የሚገኘውን የንግሥተ ሳባን የእስራኤል ጉዞና የኢየሩሳሌም ጉብኝት መሠረት በማድረግ ስለ አይሁድ ሃይማኖት (Judaism) ወደ ኢትዮጵያ መግባት፣ መስፋፋትና ብሔራዊ ሃይማኖት መሆን በዝርዝር ያስረዳል። ክብረ ነገሥት ንግሥተ ሳባ 52ኛ የኢትዮጵያ ንግሥት እንደነበረችና ንግሥተ አዜብ፣ ማክዳ በመባል እንደምትታወቅ ይገልጻል። እርሷም የሰሎሞንን ጥበብ ዝናውን ሰምታ ትጎበኘው ዘንድ ከብዙ አገልጋዮችና ጓዝ ጋር ወደ ኢየሩሳሌም እንደሄደች፤ ንጉሥ ሰሎሞንም ተቀብሎ ለተከተሏት ሰዎቿና ለጓዟ ጋዛ አክባቢ፣ ለእርሷ ደግሞ ኢየሩሳሌም ማረፊያ እንደፈቀደላት ወይም ርስት እንደሰጣት ይናገራል። ከዚህ ጊዜ ጀምሮ ኢትዮጵያውያን በቅድስት አገር ኢየሩሳሌም ዴር ሡልጣን የተባለውን የቅድስና ሥፍራ ጨምሮ ባለርቶች ሆኑ በማለት መጻሕፍት በመተባበር ይመሰክራሉ። በኢየሩሳሌም የኢትዮጵያ ገዳማት ዋና ርስት ዴር ሥልጣን (የንጉሥ/ንግሥት ርስት) የሚለውን ስያሜ ያገኘው በዚሁ ምክንያት ነው። (1ነገ፤ 10፡ 1-13፣ ማቴ፤ 12፡42) ንግሥተ ሳባ እግዚአብሔር ለሰሎሞን የሰጠውን ጥበብ ተመልክታ “እግዚአብሔር እስራኤልን ለዘላለም ወዶታልና ስለዚህ ጽድቅና ፍርድ ታደርግ ዘንድ ንጉሥ አድርጐ አስነሣህ ” (1ነገ፤ 10፡ 9) በማለት እርሱን አድንቃ ጥበብ የገለጠለትን አምላክ እግዚአብሐርን አመስግና የወደደችውን ሁሉ ከንጉሡ ተቀብላ ወንድ ልጅ ፀንሳ ታቦተ ጽዮንን ይዛ ወዳገሯ እንደተመለሰች ክብረ ነገሥት ያብራራል። ከሰሎሞን የወለደችውን ልጇንም ምኒልክ ብላ እንደሰየመችው፣ 22 ዓመት ሲሆነውም ወደ አባቱ ሀገር እንደላከችው ይገልጻል። ንጉሥ ሰሎሞንም ልጁ ቀዳማዊ ምኒልክን በሀገሩ በእስራኤል 3 ዓመት ሕገ ኦሪትን፣ ሕገ መንግሥትን አስተምሮ፣ 12000 ደቂቀ እስራኤልን፣ 22 ካህናትን ሹማምንትን ጨምሮ በእናቱ ሀገር ይነግሥ ዘንድ ወደ ኢትዮጵያ እንደላከው በክብረ ነገሥት ተጽፏል። በዚህም ምክንያት ከ1000 ዓመት (ከክ.ል.በፊት) ጀምሮ የአይሁድ ሃይማኖት በኢትዮጵያ ብሔራዊ ሃይማኖት እንደሆነ፤ የብሉይ ኪዳን መጻሕፍትም ከዕብራይስጥ ወደ ግእዝ ቋንቋ እንደተተረጎሙ ክብረ ነገሥት በሠፊው ያትታል። ለዚህም መስዋዕተ ኦሪት ይሰዋባቸው የነበሩ እንደ አከሱም፣ ተድባበ ማርያም፣ መርጡለ ማርያም፣ ጣና ቂርቆስ ያሉ ቦታዎች፤ በኢትዮጵያ ቤተክርስቲያን (በተለይም በሰሜንና ሰሜን ምዕራብ) በስፋት የሚታዩ የቤተክርስቲያን አሠራር፣ የቃል ኪዳኑ ታቦት፣ የቀዳሚት ሰንበት አከባበር፣ የሚበሉና የማይበሉ እንስሳት፣ ግዝረትና የመሳሰሉት ሃይማኖታዊና ባህላዊ ተግባራት በማስረጃነት ይጠቀሳሉ። (ክብረ ነገሥት፤ ገጽ 290-350) ቀዳማዊ ምኒልክ ወደ ሀገሩ በመጣ ጊዜ እግዚአብሔር ለሙሴ የሰጠውን የቃል ኪዳኑን ታቦት (ታቦተ ጽዮንን) ይዞ መጥቶ በአክሱም አኖራት። ስለዚህም ኢትዮጵያ የብሉይ ኪዳን መጻሕፍትና የአይሁድን ሃይማኖት ከመቀበሏም በተጨማሪ የታቦተ ጽዮን ማደሪያ ልዩ የቃል ኪዳን ሀገር እንድትሆን አድርጓታል። በዚህ ሁኔታ ብሔራዊነቱን ለክርስትና እስካስረከበበት እስከ 4ኛው መቶ ክፍለ ዘመን (ከክ.ል.በኋላ) በኢትዮጵያ ዋና ሃይማኖት ሆኖ ቆይቷል። 2.ዜና ክርስትና ኢትዮጵያ የአይሁድ ሃይማኖት ወደ ኢትዮጵያ ከገባበት ጊዜ ጀምሮ ተሳላሚዎች ለበዓላት ቢያንስ በዓመት አንድ ጊዜ ወደ ኢየሩሳሌም ይሄዱ ነበር (ሶፎ፤ 3፡10)። ይኸው ቅድስት ሀገር ኢየሩሳሌምን የመሳለም ተግባር እስከ ዘመነ ክርስትና ቀጥሎ የኢትዮጵያ ንግሥት የሕንደኬ ጃንደረባ (በጅሮንድ/የገንዘብ ሚንስትር) በ34 ዓ.ም. (ከክ.ል.በኋላ) ኢየሩሳሌምን ተሳልሞ የኢሳይያስን የትንቢት መጽሐፍ እያነበበ ወደ ሀገሩ ሲመለስ በእግዚአብሔር ፈቃድ ሐዋርያው ፊልጶስ ተልኮ አስተማረው። ጋዛ በተባለው አካባቢ ሲደርሱም “ኢየሱስ ክርስቶስ የእግዚአብሔር ልጅ እንደሆነ አምናለሁ... እነሆ ውሃ እንዳልጠመቅ የሚከለክለኝ ምንድር ነው? ” ብሎ በማመኑ ጥምቀተ ክርስትና እንደተፈጸመለትና ዜና ክርስትናን ይዞ በደስታ ወደ ሀገሩ እንደተመለሰ መጽሐፍ ቅዱስ ይናገራል (ሐዋ፤ 8፡ 26-40)። አውሳብዮስ የተባለው ታዋቂ የቤተክርስቲያን ታሪክ ፀሐፊ “Historia Ecclessia” በተሰኘው መጽሐፉ ከዕብራውያን ወገን ያልሆነ የመጀመሪያው የክርስትና ፍሬ መሆኑን ሲመሰክር፤ ወደ ሀገሩ ተመልሶ ክርስትናን ማስተማሩን ደግሞ ሄሮኒሞስ (Jerom) የተባለው የቤተክርስቲያን አባት “ጃንደረባው ለወገኖቹ ሐዋርያ ሆነ ” በማለት ገልጧል። ኢትዮጵያ በነበራት መልክአ ምድራዊ አቀማመጥ ምክንያት በወቅቱ ይነበረው አክሱማዊ መንግሥት ከሰሜን አፍሪቃ፣ ሜዲትራንያን፣ መካከለኛው ምሥራቅ እንዲሁም ከሩቅ ምሥራቅ አገሮች ጋር ጠንካራ የንግድን የባህል ግኝኙነት እንደነበረው ይታመናል። በ2ኛውና በ3ኛው መቶ ክ/ዘመን የነዚሁ አገሮች ነጋዴዎች በተለይም ከግሪክ፣ ከፋርስ፣ ከአርመን፣ ከሶርያ፣ ከሕንድና ከሌሎችም አገሮች የሚመጡ ክርስቲያን ነጋዴዎች አክሱም፣ ምጽዋና አዱሊስ አካባቢ ይኖሩ እንደነበርና ክርስትያኖቹ ነጋዴዎች ቤተጸሎት መሥርተው ክርስትናቸውን ያካሂዱ እንደነበር ይታመናል። በዚህም ምክንያት በጃንደረባው የተሰበከው ዜና ክርስትና እንዲጠናከር ማገዙን አንዳንድ የታሪክ ምሁራን ይገልጻሉ። ምንም እንኳን ክርስትና ከ34 ዓ.ም. ጀምሮ የተሰበከ ቢሆንም ክርስትና እየተስፋፋ የሄደው ከ4ኛው መቶ ክ/ዘመን ጀምሮ በፍሬምናጦስ (አባ ሰላማ ከሳቴ ብርሃን) ከፍተኛ ጥረት ነው። ፍሬምናጦስና ኤደስዮስ የተባሉ ክርስቲያን ወጣቶች ሜሮጵዩስ ከሚባል አጐታቸው ጋር ከአገራቸው ከጢሮስ ወደ ሕንድ ሲጓዙ አዱሊስ አካባቢ ሜሮጵዮስና ሌሎች ተጓዦች በአደጋ ጣዮች እንደተገደሉ፣ ፍሬምናጦስና ኤደስዮስ ወደ ንጉሡ አል-አሜዳ እንደወሰዷቸው፣ ንጉሡም ከልጆቹ ከኢዛና እና ሳይዛና ጋር እንዳሳደጋቸው፣ በዕድሜና በጥበብ የሚልቀውን ፍሬምናጦስን ፀሐፊ፣ ኤደስዩስን ደግሞ መጋቢ አድርጎ እንደሾማቸው፣ እነርሱም ክርስትና ሃይማኖትን ለንጉሡ ልጆች እንዳስተማሯቸው ሩፊኖስ፣ ቴዎደሬት፣ ሶቅራጥስ እና ሶዞሜን የተባሉ የታሪክ ፀሐፊዎች በመተባበር ይመሰክራሉ። 3.ክርስትና በኢትዮጵያ ብሔራዊ ሃይማኖት እንደሆነ ኢዛና እና ሳይዛና በ290 ዓ.ም. አካባቢ ነገሡ። ኤደስዩስ ወደ አገሩ ወደ ጢሮስ ተመለሰ። ፍሬምናጦስ ግን ኢትዮጵያዊነትን መርጦ በአክሱም ኖረ። የኢትዮጵያ ክርስትና ክህነት እንደሚያስፈልገው ለነገሥታቱ በነገራቸው ጊዜ በወቅቱ ቅርብ ከነበረችው የእስክንድርያ ቤተክርስቲያን ጳጳስ እንዲያመጣላቸው ወደ ግብጽ ተላከ። 20ኛው የእስክንድርያ ቤተክርስቲያን ፓትርያርክ አባ አትናቴዎስ “መንፈስ ቅዱስ ያደረበት፣ ይህን ተልዕኮ ሊፈጽም የሚችል ከአንተ በላይ ማንን እናገኛለን " በማለት አባ ሰላማ፣ ጳጳስ ዘአክሱም ወለኩላ ኢትዮጵያ ብሎ ሹሞ ሰደደው፣ የመጀመሪያው የኢትዮጵያ ቤተክርስቲያን ጳጳስ ሆነ። ከዚህም በኋላ ኢዛና እና ሳይዛና (አብርሃና አጽብሃ) ክርስትናን ተቀበሉ፣ ክርስትናም የሀገሪቱ ብሄራዊ ሃይማኖት ሆነ። አባ ሰላማ የግዕዝን ቋንቋ ጠንቅቆ የሚያውቅ ስለነበር የቀድሞውን ሳባዊ ፊደል የአቀማመጥ፣ አጻጻፍና አናባቢዎችን አሁን በምንጠቀምበት መልክ አስተካክሎ የቀመረው እርሱ ነው። የሐዲስ ኪዳን መጻሕፍትን ከሀገሩ ቋንቋ ከሱርስት (Syriac) እና በዘመኑ ዓለም አቀፍ ከነበረው ከግሪክ ቋንቋ ወደ ግእዝ ተረጐመ። ቤተ ቀጢን የተባለውን የመጀመሪያውን የአክሱም ትምህርት ቤት መሠረተ። ከጢሮስ ይልቅ ኢትዮጵያን እንደ ትውልድ ሀገሩ፣ ከሶርያውያን ይልቅ ኢትዮጵያውያንን ወገኖቹ አድርጐ የክርስትናን ብርሃን በመላው ኢትዮጵያ እንዲበራ በማድረጉ የኢትዮጵያ ቤተክርስቲያን “ከሳቴ ብርሃን” (ብርሃን ገላጭ) ብላ ትጠራዋለች። 4.ምንኩስና በኢትዮጵያ እንደተስፋፋ በጃንደረባው የተሰበከችው፣ በአቡነ ሰላማ ከሳቴ ብርሃን የተስፋፋችውና ብሔራዊ ተቀባይነትን ያገኘችው የኢትዮጵያ ቤተክርስቲያን ከቢዛንታይን ግዛት በመጡ ዘጠኝ መነኮሳት የበለጠ መጠናከር ብቻ ሳይሆን ገዳማዊ ሕይወት (ምንኩስና) በቀዳሚነት ከተስፋፋባቸው ጥቂት አብያተክርስቲያናት ጐን ለመሰለፍ በቅታለች። በ4ኛውና በ5ኛው መቶ ክፍለ ዘመን በአብያተክርስቲያናት መካከል በተነሳው የዶክትሪን ልዩነትና ክርክር ምክንያት በቢዛንታይን ነገሥታትና በመለካውያን ከፍተኛ ስቃይና መከራ የደረሰባቸው የተዋሕዶ ክርስትና አባቶችና ተከታዮቻቸው ነፍሳቸውን ለማትረፍ ተሰደዱ። በተለይም ከኬልቄዶን ጉባኤ በኋላ መከራና ስደት ከጸናባቸው የተዋሕዶ ክርስትና ተከታይ አባቶች መካከል ዘጠኝ መነኮሳት ከሶርያ፣ ታናሽ እስያና ቁስጥንጥንያ ተሰደው የተዋሕዶ ክርስትና ብሔራዊ ሃይማኖት የሆነባትና ዝናዋ በመላው የክርስቲያን ዓለም የተሰማውን ኢትዮጵያን መርጠው በ480 ዓ.ም. አካባቢ መጡ። ሕዝቡም ነገሥታቱም በደስታ ተቀበሏቸው። ስለዚህም ወደ ኢትዮጵያ ሲመጡ በእግረ መንገድ ግብጽ የተማሩትን ገዳማዊ ሕይወት (ምንኩስና) በአክሱምና በአካባቢዋ አስፋፍተዋል። ለምሳሌም የመጀመሪያው የኢትዮጵያ የክርስቲያን ገዳም ደብረ ዳሞ በአባ አረጋዊ (ዘሚካኤል) በ450 ዓ.ም. የተመሠረተ ነው። እንዲሁም በአቡነ ሰላማ የተጀመረውን የሐዲስ ኪዳን መጻሕፍት ትርጓሜ በስፋት አከናውነዋል። ስለዚህም ለክርስትና መስፋፋት ባበረከቱት ከፍ ያለ አስተዋጽኦ የኢትዮጵያ ቤተክርስቲያን ተትረርገጓተስዓቱ ቅዱሳን (ዘጠኙ ቅዱሳን) ብላ የቅድስና ማዕርግ ሰጥታ ስታከብራቸው ትኖራለች። በ6ኛው መቶ ክፍለ ዘመን የኢትዮጵያ (የአክሱም) መንግሥት ቀይ ባሕርን ተሻግሮ እስከ ደቡብ ዓረብ (የመን) ድረስ ግዛቱን አስፍቶ እንደነበር ይታመናል። ከ495-525 ዓ.ም. የነገሠው አጼ ካሌብ በየመን (ናግራን/Najran) አካባቢ የሚገኙ ክርስቲያኖች ድሁ ንዋስ (ፊንሐስ) በተባለ አይሁዳዊ ከደረሰባቸው ጥቃት ለመከላከል 120000 ሠራዊት በ60 መርከቦች አዝምቶ ከጥቃት ታድጓቸዋል። አጼ ካሌብ ከየመን በድል ከተመለሰ በኋላ ድል ያቀዳጀውን ክርስቶስን አመስግኖ፣ አክሊለ ንግሡን (ዘውዱን) ወደ ኢየሩሳሌም ለመታሰቢያ ልኮ፣ ልጁ ገብረ መስቀልን በምትኩ አንግሦ ቀሪ ሕይወቱን ከዘጠኙ ቅዱሳን አንዱ አባ ጰንጠልዮን አክሱም አካባቢ በመሠረቱት ገዳም በምናኔ አሳልፏል። አስካሁን እንደተመለከትነውና ወደፊትም እንደምናየው ክርስትና ከተራው ሕዝብ አልፎ በቤተመንግሥት ላይ የነበረውን ተጽእኖ ነው። ከዚህም የተነሳ ነገሥታቱና መኳንንቱ ሳይቀሩ በክርስትና ሕይወት ይመሰጡና ለምናኔ ይበቁ እንደነበርም እናስተውላለን። ለምሳሌም የአጼ ገብረ መስቀል ልጅ (የአጼ ካሌብ የልጅ ልጅ) አባ ሙሴ የአያቱን የአጼ ካሌብን ፈለግ ተከትሎ በምናኔ (በምንኩስና) ይኖር እንደነበረ የመጨረሻ የሕይወት ዘመኑንም በኢየሩሳሌም የኢትዮጵያውያን ገዳም (ዴር ሥልጣን) እንዳሳለፈ ይነገራል። 5.የቅዱስ ያሬድ ዜማ የኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋሕዶ ቤተክርስቲያን ለምስጋና የምትገለገልበትን ዜማ የደረሰው ቅዱስ ያሬድ ነው። ቅዱስ ያሬድ ሚያዚያ 5 ቀን 505 ዓ.ም. አክሱም ከተማ ውስጥ ከአባቱ ከአብዩድ ከእናቱ ከታውክልያ ተወለደ። ቅዱስ ያሬድ የአብ የወልድ የመንፈስ ቅዱስ ምሳሌዎች በሆኑ በሦስት ሥልት በግዕዝ፣ በእዝልና በአራራይ ተከፍለው የሚዜሙ ዜማዎችን ያካተተ መዝገበ ድጓን አዘጋጀ። ሌሎችንም የዜማ መጻሕፍት ጻፈ። ለዜማው መለያ የሚረዱ 10 ምልክቶችንም አዘጋጀ። አንዳንድ የቤተክርስቲያን ሊቃውንት ስምንቱን ምልክቶች ቅዱስ ያሬድ እንዳዘጋጀና ሌሎቹን ሁለቱን የኋላ ሊቃውንት እንደጨመሩ ይገልጣሉ። ቅዱስ ያሬድ በመንፈስ ቅዱስ አጋዥነት ይህን ወደር የሌለው ዜማ ከነምልክቱ የቀመረው በምዕራባውያን ዘንድ እጅግ በጣም የሚደነቁት እንደሞዛርት ያሉት የዜማ ሰዎች በ14ኛው መቶ ክፍለ ዘመን የዜማ ምልክት ከመቅረጻቸው ከ800 ዓመታት በፊት ነው። ይህም የቅዱስ ያሬድን ዜማና የቤተክርስቲያኗን ቀደምትነት ይገልጻል። ከዚህም በላይ ከአጼ ካሌብ ልጅ ከአጼ ገብረ መስቀል ጋር ሆኖ ሐዋርያዊ ጉዞ በማድረግ ክርስትናን ከአክሱም በስተደቡብ ባለው የኢትዮጵያ ክፍል አስፋፍቷል። እዚህ ላይ ልናስተውለው የሚገባ ዓቢይ ጉዳይ ቢኖር በኢትዮጵያ የክርስትና አመጣጥና መስፋፋት ሦስት ዋና ነገሮች መኖኦሩን ነው። ይኸውም ዜና ክርስትና በኢትዮጵያዊው ጃንደረባ፣ ክህነት በአቡነ ሰላማ ከሳቴ ብርሃን፣ ገዳማዊ ሕይወት በተስዓቱ ቅዱሳን የተከናወነ ሲሆን፤ ክርስትና ወደ ኢትዮጵያ የመጣውና የተስፋፋው ከሌሎች አገሮች በተለየ መልኩ የአንድም ሐዋርያ ደም ሳይፈስ በሰላማዊ መንገድ ከላይ ከቤተመንግሥት ወደ ሕዝብ መሆኑን እንድናስተውለው ይገባል። 6.ክርስትና በመላው ኢትዮጵያ መስፋፋቱና የቤተክርስቲያን ዕድገት 6.1.ሥነ-ሕንጻ በእስልምና መነሳትና በዮዲት ጥቃት ምክንያት የተዳከመው የአክሱም መንግሥት ኃያልነቱና ገናናቱ እየቀዘቀዘ ሄዶ በመጨረሻ ከ10ኛው መ/ክ/ዘ መጀመሪያ እስከ 13ኛው መ/ክ/ ዘ መገባደጃ ድረስ ቦታውን ለዛጉዌ ሥርወ መንግሥት ለቀቀ። በአንጻሩም በዮዲት ጥቃት ምክንያት እጅግ ተዳክሞ የነበረው ክርስትና እንደገና ማንሰራራትና መስፋፋት ጀመረ። የዛጕዌ ነገሥታት ከሚታወቁባቸው ነገሮች ዋናው ከአንድ ዐለት ተፈልፍለው የታነጹ ውቅር አብያተክርስቲያት ናቸው። በተለይም በቅዱስ ላልይበላ የታነጹት 11 አብያተክርስቲያናት በዓለም ከሚታወቁ ሰባት አስደናቂ ነገሮች በላይ የሚያስደንቁ መሆናቸውን ምዕራባውያን አገር ጐብኚዎች ሳይቀሩ ይመሰክራሉ። 6.2.ሥነ-ጽሑፍ ከ330 ዓመት የዛጉዌ መንግሥት በኋላ በ1270 ዓ.ም. በደብረ ሐይቅ ከአባ ኢየሱስ ሞአ የተማረው አጼ ይኩኖ አምላክ ነገሠ። ከዚህ ጊዜ ጀምሮ በ1966 ዓ.ም. እስከቀረበት ድረስ ቤተክርስቲያን ሢሶ (1/3) መንግሥት (ርስት) ባለቤት ሆና ቆይታለች። ከአጼ ይኩኖ አምላክ ጀምሮ እስከ ግራኝ ወረራ ድረስ ያለው ጊዜ የገዳማትና የአብነት ት/ቤቶች መስፋፋት፣ የሥነጽሑፍ ዕድገት የታየበት ጊዜ ነበር። በዚህ ጊዜ ራሳቸው ነገሥታቱ ሳይቀሩ ብዙ መጻሕፍትን ይጽፉ ነበር። ለምሳሌም አጼ ዘርዓ ያዕቁብ (1426 - 1440) መጽሐፈ ብርሃን፣ መጽሐፈ ምዕላድ፣ ጦማረ ትስብእት፣ ክህደተ ሰይጣን፣ መጽሓፈ ባህርይ፣ ተዓቅቦ ምሥጢርና እግዚአብሔር ነግሠ የተባሉትን መጻሕፍት ከመሳፋቸውም በላይ ሊቃውንተ ቤተክርስቲያን ሃይማኖትን የሚያስፋፉ ምግባራትን የሚያጸኑ ልዩ ልዩ ድርሰቶችን እንዲጽፉ ያበረታቱ ነበር። ከሊቃውንትም እነአባ ጊዮርጊስ ዘጋስጫ መጽሐፈ ምሥጢር፣ ሰዓታትና አርጋኖን የተባሉትን መጻሕፍት የጻፉት በዚሁ ጊዜ ነው። 6.3.የአብነት ትምህርት ቤቶች በኢትዮጵያ ቤተክርስቲያን ነገሥታቱና ልጆቻቸው ሳይቀሩ ይማሩ ያስተምሩ ነበር። ሀገራችን በአፍሪካ ውስጥ ብቸኛዋ የራሷ ፊደል፣ ቁጥርና ቋንቋ እንዲኖራት ያደረገች ቅድስት ቤተክርስቲያናችን ናት። በ1268 ዓ.ም. የነገሠው አጼ ይኩኖ አምላክ በአባ ኢየሱስ ሞአ እንደተማረ ታሪክ ያስረዳል። ከአጼ ፋሲለደስ ጀምሮ ለ140 ዓመታት ያህል የተፈራረቁ የጎንደር ነገሥታት አብያተ ክርስቲያናትንና አብያተ መንግሥትን በማነጽ፣ መጻሕፍትን በማጻፍ፣ የአብነት (የትርጓሜ) ትምህርት ቤቶችን በማስፋፋት በሚስዮናውያን ምክንያት በተከሰተው ጦርነትና ዕልቂት ደረሰውን ጉዳት ክሰዋል። ከ1632 ዓ.ም. በኋላ ወደ 200 ዓመታት ለሚጠጋ ጊዜ በሀገሪቱም ሆነ በቤተክርስቲያን ከፍ ያለ ዕድገት ታይቷል። 6.4.የአገር አንድነትና የጵጵስና መምጣት ከ1770-1855 ዓ.ም. የቆየው የዘመነ መሳፍንት የርስ በርስ ጦርነት አክትሞ ዳግማዊ አጼ ቴዎድሮስ ሀገሪቱን አንድ ለማድረግ ሲነሱ በመሳፍንት ድጋፍ የሚንቀሳቀሱ ሚስዮኖችን ከአገር አባረሩ። ከ1855-1869 የተነሱት አጼ ቴዎድሮስም ሆኑ ከሳቸው ቀጥለው የነገሡት አጼ ዮሐንስ ኢትዮጵያን ከተዋሕዶ ሃይማኖት፤ ተዋሕዶ ሃይማኖትን ከኢትዮጵያ ነጥለው የማያዩ ሃይማኖታውያንና ብሔራውያን መሪዎች ነበሩ። በየዘመናቸው በኢትዮጵያ የነበሩትን ሚስዮናውያንን ሁሉ ሰብስበው “ኢትዮጵያ የራሷ የወንጌል መምህራን አሏት፤ ይልቁንስ እናንተ የሠልጠናችሁበትን ለኛ የሚያስፈልገንን ሥልጣኔ ቴክኖሎጂ አስትምሩ” ብለዋቸው እንደነበር ብፁዕ አቡነ ጎርጎርዮስ (1932-1982) የኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋሕዶ ቤተክርስቲያን ታሪክ በትሰኘ መጽሐፋቸው ገልጸውታል። ዳግማዊ አጼ ምኒልክም በበኩላቸው በመሳፍንት ተከፋፍላ የነበረችውን ኢትዮጵያን አንድ ለማድረግ እጅግ አድርገው የደከሙ የቀደምቶቻችውን የአፄ ቴዎድሮስንና የአፄ ዮሐንስን ዓላማ በመከተል የደቡብ ኢትዮጵያን ግዛት ሲያስሱ ከግራኝ ወረራ ጀምሮ ጠፍተው የነበሩ አብያት ክርስቲያናትንና ገዳማትን እንዲታደሱ አድርገዋል። የኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋሕዶ ቤተክርስቲያን በራሷ ልጆች (ጳጳሳት) እንድትተዳደር፣ ከራሷም ሊቃውንት መካከል ጳጳሳት እንዲሾሙላት ከዛጉዌ ነገሥታት መካከል በቅዱስ ሀርቤ የተጀመረው ጥረት እየተነሳ እየወደቀ እስከ ግርማዊ ቀዳማዊ አጼ ኃይለ ሥላሴ ዘመነ መንግሥት ደርሷል። አጼ ኃይለ ሥላሴ ከግብጽ እስክንድርያ ቤተክርስቲያን ጋር ባደረጉት ትዕግሥት የተሞላበት ድርድርና ውይይት በኋላ በ1951 ዓ.ም. ቅድስት ቤተክርስቲያናችን የመጀመሪያውን ፓትርያርክ አቡነ ባስልዮስን ለመሾም በቅታለች። ነገር ግን ቤተክርስቲያኗ ይህን በራሷ ሊቃውንት የመተዳደር እድል አግኝታ 20 ዓመት እንኳን ሳይሞላ በ1967 ዓ.ም. የሁለተኛው ፓትርያርክ መገደል እጅግ በጣም አሳዛኝ የታሪክ ጠባሳ ጥሎ አልፏል። ይባስ ብሎ በ1984 ዓ.ም. የ4ኛው ፓትርያርክ መሰደድ ቤተክርስቲያኗን ከፍተኛ ፈተና ላይ ጥሏታል። 7.የኢትዮጵያ ቤተክርስቲያን ያጋጠሟት ችግሮች 7.1. የዓረቦች ጥቃት መሐመድ ነቢይ ነኝ ብሎ በተነሳበት ወቅት ቀረይሽ የተባሉ የዓረቢያ ነገዶች ስለተቃወሙት ከመካ ወደ መዲና ሲሰደድ ከተከታዮቹ ጥቂቶች በተደጋጋሚ ወደ ኢትዮጵያ ሸሽተው የተደረገላቸውን ሰብአዊ ርህራሄ ሰምቶ “አበሻን አትንኩ” ብሎ መናዘዙ ይነገራል። ይሁን እንጂ ብዙም ሳይቆይ ተከታዮቹ ይህንን የነቢያቸውን ቃል ባለማክበር ኢትዮጵያን መውጋት ጀመሩ። በተጨማሪም ኢትዮጵያውያን ለንግድና ተለያዩ ተግባሮች ወደ ግብጽ፣ ወደ ኢየሩሳሌም፣ ወደ ቢዛንታይን፣ ወደ ሮም፣ ወደ ሕንድ ወዘተ. የሚጓዙበትን የየብስ መንገድና በቀይ ባህር አካባቢ የነበሩትን የአዱሊስንና የምፅዋን ወደቦች፣ የዳሕላክ ደሴቶችን በኃይል በመንጠቅና በማውደም ከ8ኛው መቶ ክ/ዘ ጀምሮ አገራችንም ሆነ ቤተክርስቲያናችን ከውጪው ዓለም ጋር ያላቸው ግንኙነት እንዲቋረጥ አደረጉ። እንደ ሮም፣ ቢዛንታይን፣ ፋርስና ቻይና ኃያል የነበረው የአክሱም መንግሥትና ብሔራዊ ሃይማኖት የነበረው ክርስትናም በብዙ መከራ ለማለፍ ተገደደ። 7.2. ዮዲት ጉዲት ያደረሰቸው ጥፋት ከአብርሃና አጽብሃ ዘመነ መንግሥት ጀምሮ ክርስትና የመንግሥት ሃይማኖት በመሆኑ እየተስፋፋና እየተጠናከረ ሲሄድ ቀደም ሲል የአይሁድን እምነት ይከተሉ ከነበሩት ቤተ እስራኤሎች ከፊሎቹ ክርስትናን አንቀበልም በማለታቸው በየጊዜው ከደረሰባቸው እንግልት ለማምለጥ ከአክሱምና ከአካባቢዋ ርቀው ተሰደዱ። ሆኖም በሚኖሩባቸው አካባቢዎች ከጊዜ ወደ ጊዜ ዘራቸው እየበዛ ሄደ። በ9ኛው መቶ ክ/ዘ ለክርስቲያኑ የአክሱም መንግሥት ግብር ላለመገበር ወስነው አክራሪ ይሁዲ በነበረችው በአገው ተወላጇ በዮዲት (ጉዲት) (842-882) መሪነት በመንግሥት ላይ አመጹ። ወዲያውም መንግሥትን በኃይል ከያዙ በኋላ አክሱምን አወደሙ። በአብርሃና አጽብሃ የተሠራችውንና በ12 ጉልላት የተጌጠችውን የመጀመሪያዋን የአክሱም ጽዮን ቤተክርስቲያን አፈረሱ፤ ስፍር ቁጥር የሌላቸውን መጻሕፍት አቃጠሉ፣ ሐውልቶችንም ሰባበሩ፣ ቁጥራቸው ብዙ የሆነ ካህናትና ምዕመናንን ገደሉ። በዚህ አኳኋን ክርስትና ኢትዮጵያ ከገባበት ጊዜ ወዲህ የመጀመሪያው ስደትና መከራ ተፈጸመ። በዚህም ጊዜ ታቦተ ጽዮን ተሰዳ ዝዋይ ደሴት በደብረ ጽዮን ለ40 ዓመታት ቆየች። 7.3. የግራኝ ወረራ የወቅቱ ታላቅ እስላማዊ ኃይል ኦቶማን ቱርኮች መላዋ ሰሜን አፍሪቃና የአውሮጳን ደቡባዊ ክፍል ግሪክ፣ ስፔን፣ አልባንያ፣ ቡልጋርያ፣ ሩማንያና ዩጎዝላቪያን በቀላሉ ሲቆጣጠሩ ሃገራችን ኢትዮጵያ ግን አልተደፈረችም ነበር። ነገር ግን የአዳል ኢማም የነበረው በኢትዮጵያ ምሥራቃዊ ክፍል የተወለደው ግራኝ መሐመድ በስመ እስላም ከቱርክ ባለሥልጣኖች ጋር ተመሳጥሮ የኢትዮጵያን ክርስቲያን መንግሥት ወግቶ ሕዝበ ክርስቲያን ለመደምሰስና ሀገሪቱን ለቱርክ ለማስረከብ ተነሳ። በኦቶማን ቱርክ ኃይሎች እገዛ የአጼ ልብነ ድንግልን መንግሥት ወግቶ አብዛኛውን የሀገሪቱን ክፍል ያዘ። ከ1519 እስከ 1543 ዓ.ም. ድረስ በጠቅላላው ለ15 ዓመታት ያህል ከሐረር እስከ ጐንደር፣ ከጀምጀም እስከ አክሱም ያሉ አብያተክርስቲያናትን እያቃጠለ፣ ውድና ብርቅ የሆኑ በአልማዝ በዕንቁ፣ በወርቅ የተጌጡ ንዋያተ ቅድሳትን እየዘረፈ፣ ካህናትን ምእመናንን በግድ እያሰለመ፣ ያልሰለመውንም በጭካኔ እያረደ ይህ ነው የማይባል ከፍተኛ ውድመት አደረሰ። ጦርነቱን መቋቋም ያቃተው የአጼ ልብነ ድንግል መንግሥት የወቅቱን የክርስቲያን ኃያል የፖርቱጋል መንግሥት ለእርዳታ ቢለምንም በብዙ ምክንያት አፋጣኝ መልስ ባለመገኘቱ ጉዳቱ ማቆሚያ ያጣ ሆነ። በዚሁም ጊዜ የአክሱም ጽዮን ባለ 7 ጉልላት ቤተክርስቲያንና የሐይቅ እስጢፋኖስ ገዳምን ጨምሮ በሺህ የሚቆጠሩ ገዳማትና አድባራት እንዳልነበሩ ሆኑ። ካህናትና መነኮሳትም ገዳማቸው ሲቃጠል ሲያዮ በብስጭት እሳት ውስጥ እየገቡ አረው አለቁ። የሃይማኖት መጻሕፍትና የታሪክ ሰነዶች የእሳት ራት ሆኑ። ንጉሡም ከአንዱ ቦታ ወደሌላው ሲሸሹ ቆይተው በመጨረሻ ደብረ ዳሞ ላይ አረፉ። ከአባቱ ይልቅ እጅግ በጣም አስተዋይና ጥበበኛ፤ ደፋርና ጀግና የነበረው የአጼ ልብነ ድንግል ልጅ ወጣቱ አጼ ገላውዴዎስ ነገሠ። አጼ ገላውዴዎስም የፖርቱጋልንና የራሱን ወታደሮች በማስተባበር ግራኝን ቆላ ድባ በተባለ ቦታ ድል አደረገ። የ15 ዓመቱ ሰቆቃ አብቅቶ አብያተክርስቲያናት እንደገና ተሠሩ፣ መጻሕፍት ተጻፉ፣ ከሞት የተረፉት ምእመናን በተጽእኖ ከተቀበሉት እስልምና እየተመለሱ በክርስትና እምነታቸው ጸኑ፣ ተጽናኑ። ነገር ግን የግራኝ ወረራ ጥሎት የሄደው ከፍተኛ የሞራል፣ የምግባርና ሌሎችም ችግሮች በቀላሉ የሚወገዱ አልሆኑም። ለምሳሌም ብፁእ አቡነ ጐርጐርዮስ “የኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋሕዶ ቤተክርስቲያን ታሪክ” በተሰኘው መጽሐፋቸው እንደገለጡት የግራኝ ወረራ በቤተክርስቲያናችን ላይ ከጣላቸው መካከል የቤተክህነት የሙያ ደረጃ ዝቅ ማለት፣ ያለካህን ፈቃድ ማግባት (ዕቁባት ማስቀመጥ)፣ በሆነው ባልሆነው ባል ከሚስቱ (ሚስት ከባሏ) መፋታት፣ ጥቂቶቹ ናቸው። ከዚህም በላይ የሚስዮናውያን በቀላሉ መስፋፋት፣ የቱርክ የጦርነትና የወረራ ሙከራ፣ የግብጽ ተደጋጋሚ ጥቃት፣ የደርቡሽ የጥፋት ዘመቻ፣ የእስልምና መስፋፋት፣ እና የመሳሰሉት ችግሮች በሙሉ የግራኝ ወረራ ያመጣቸው መከራዎች ናቸው። 7.4. የሚስዮናውያን ዘመቻ ከአጥፊው የእስላም ኃይል ጋር በተደረገው ጦርነት እንዲረዱን በክርስትና ወንድማማችነት (Ecumenism) መንፈስ የተጠሩት የፖርቱጋል ኃይሎች ከኢትዮጵያ ወታደሮች ጋር ተባብረው ግራኝን ድል በማድረግ ባለውለታ በመሆናቸው ምክንያት ለቤተመንግሥት የነበራቸውን ቅርበት በመጠቀም የኢትዮጵያ ቤተክርስቲያንን እምነቷን አስለውጠው በኃይል በሮማ ካቶሊክ ሥር ለማዋል ከፍተኛ ትግል ማካሄድ ጀመሩ። በተለይም ኢየሱሳውያን (Jesuits) የተባሉ የካቶሊክ ሚስዮናውያን ከ1604-1632 ዓ.ም. የነገሠውን አጼ ሱስንዮስን አግባብተውና አታለው የካቶሊክን ሃይማኖት እንዲቀበል አደረጉ። ንጉሡም የካቶሊክ ሃይማኖት ብሔራዊ ሃይማኖት ይሁን ብሎ በይፋ አወጀ፣ የካቶሊክን ሃይማኖት የማይቀበል ሁሉ እንዲገደል አዘዘ። በዚህም ምክንያት “ሰማዕትነት አያምልጥህ” እየተባባለ ከበጌምድር፣ ከስሜን፣ ከትግሬ፣ ከሸዋ፣ ከላስታ፣ ከጎጃም እና ከሌሎችም የሀገሪቱ ክፍሎች ተጠራርቶ ጐንደር ገብቶ ስፍር ቁጥር የሌለው ሕዝብ አለቀ። ንጉሡ አጼ ሱስንዮስ እና ሠራዊቱ በአንድ ወገን፣ ሕዝቡና ካህናቱ በሌላ ወገን ሆነው ለዓሥር ዓመታት ያህል ባደረጉት የሃይማኖት ጦርነት ብዙ ነፍስ ጠፋ፣ በአንድ ቀን ብቻ ከ8000 በላይ የሚሆኑ ሰዎች ሞቱ። ከዚህ ሁሉ ጦርነትና እልቂት በኋላ ነገሩ እየተባባሰ ከመሄዱ በቀር ምንም እንዳልተቀነሰ በመመልከት ንጉሡ አጼ ሱስንዮስ በ1632 ዓ.ም. “ፋሲል ይንገሥ፣ ሃይማኖት ይመለስ” ብሎ አዋጅ አስነግሮ ዘውዱን ለልጁ ለፋሲለደስ አውርሶ በምናኔ ወደ ጣና ገዳማት ሄዶ ብዙም ሳይቆይ አረፈ። የአጼ ፋሲለደስ የመጀመሪያ እርምጃ የርስ በርስ ጦርነትና የእልቂት ምክንያት የሆኑትን ኢየሱሳውያንን ጠራርጐ ከአገር ማስወጣት ነበር። ይሁን እንጂ አልፎንሶ መንዴዝ (Alfonso Mendez) የተባለው ሚሲዮናዊ አድዋ አካባቢ በምትገኝ ፍሬሞና በተባለች ቦታ ተደብቆ እምነቱን ሲያስፋፋ ቆየ። አጼ ፋሲለደስ ሁኔታውን ስለሰማ ከዚያም አባረረው። እርሱ ግን እንደገና ምጽዋ ተደብቆ ቆረንጭ መናፍቅ ተክለ ሃይማኖትና ኤዎስጣቴዎስ የተባሉ ሁለት ከሃድያንን “ጸጋ” እና “ቅባት” የተባለ የኑፋቄ ትምህርት አስተምሮ ለክፍፍልና ለውዝግብ አጋልጧት ወጥቷል። ከ1520 ጀምሮ አጼ ፋሲለደስ እስከነገሡበት 1632 ዓ.ም. ድረስ መጥተው የካቶሊክን ሃይማኖት በኢትዮጵያ ለማስፋፋት በጣም ከተጣጣሩ ሚስዮናውን በመካከል ቤርሙዴዝ (ከ1520-1526)፣ ኦቭየዶ (በ1557)፣ ጰጥሮስ ፓኤዝ (ከ1603-4)፣ አልፎንሶ መንዴዝ (ከ1624-33) የተባሉት ኢየሱሳውያን ሚሲዮኖች (Jusuit Missioners) ዋና ዋናዎቹ ናቸው። 7.5. የዘመነ መሳፍንት የእርስ በርስ ጦርነት ዘመነ መሳፍንት እየተባለ በሚጠራው የጨለማ ዘመን የበጌምድር፣ የትግሬ፣ የጎጃም፣ የላስታ፣ የሸዋ፣ የኦሮሞ መሳፍንት በየወገናቸው ተነሡ። ከየጐጡ የተነሱ ኃያላን መሳፈንት የየጁ ወረሴሆችን ለምልክት ያህል በጎንደር ቤተመንግሥት ንጉሠ ነገሥት ብለው አስቀምጠው፣ ግዛት ለማስፋትና የቤተመንግሥቱ ሞግዚት ለመሆን እርስ በርስ ባደረጉት ከፍተኛ ጦርነት ሀገሪቱ ተከፋፈለች። በአንጻሩም እነዚሁ መሳፍንት ግዛት ለማስፋት ለሚያደርጉት ጦርነት የጦር መሳሪያ ዕርዳታ ለማገኘት ይረዳን ይሆናል በሚል ተስፋ በየፊናቸው ከምዕራባውያን ጋር ድርድር ጀመሩ። መሳፍንቶቹ ከምዕራባውያን ጋር ለሚያደርጉት ድርድር መልዕክተኛ ሆነው ይጠቅሙናል በማለት ሚስዮናውያንን ማቅረብ፣ ሃይማኖታዊ ተልዕኳቸውንም እንዲፈጽሙ ፈቃድ መስጠት ጀመሩ። በዚህም መሠረት ለረጅም ጊዜ አቁሞ የቆየው የሚስዮናውያን መምጣት እንደገና ተጀመረ። ይህን በሀገሪቱ የተፈጠረውን ቀውስና ጦርነት ተጠቅመው ከ1800-1860 ዓ.ም. ድረስ ወደ ኢትዮጵያ ከመጡ ሚስዮናውያን መካከል፦ በ1838 ዓ.ም. የመጣውና አድዋ አካባቢ ያስተምር የነበረው ጁሴፔ ሳፔቶ (Jusepe Sapeto) እና ከ1839 ዓ.ም. ጀምሮ የካቶሊክን እምነት ለማስፋፋት ከፍተኛ ሥራ የሠራው፣ ኋላም ላደረገው ከፍ ያለ ውለታ የሮማ ካቶሊካዊት ቤተክርስቲያን አባ ያዕቆብ ብላ ካርዲናልነት የሾመችውና የወቅቱ የካቶሊክ ሚሽን መሪ የነበረው ጀስቲን ደ ጃኮብ (Justin De Jacob) የተባሉት የስፔንና የጣልያን አልዓዛራውያን (Lazarists)፣ በ1846 ዓ.ም. የመጣውና በደቡቡ የሀገራችን ክፍል በተለይም በኦሮሚያ አካባቢ የካቶሊክን ሃይማኖት በማስፋፋት የሚታወቀው ጉሌልሞ ማሳያ (አባ ማስያስ) በግንባር ቀደምትነት የሚጠቀሱ ናቸው። በዘመነ መሳፍንት በተከሰተው የውስጥ ክፍፍልና የእርስ በርስ ጦርነት ምክንያት መሳፍንቱ ያላቸውን የበላይነት ፍላጎት ለማሳካት ሲሉ በተለያየ ጊዜ በቀጥታ በሃይማኖት ተልዕኮም (Evangelical Mission) ሆነ በአገር ጉብኝት፣ በታሪክና የመልክአ ምድር ምርምር ስም ወደ ሀገሪቱ የሚገቡ አውሮጳውያን እየተበራከቱ መጡ። ቀደም ሲል ይታወቁ የነበሩት የካቶሊክ ሚስዮኖች ብቻ ሳይሆን የተለያዩ የፕሮቴስታንት ሰባኪዎችም መግባት ጀመሩ። ምንም እንኳን መሳፍንቱ ከአውሮጳ አገሮች ጋር በተለይም ከጣልያንና ከፈረንሳይ ጋር ግንኙነት ለማድረግ ይረዱናል ብለው ቢቀበሏቸውም ሕዝቡና ካህናቱ ግን እጅግ አድርገው ይቃወሟቸው ነበር። በዚህ ዘመን ከመጡ የፕሮስቴንታንት ሚስዮኖች መካከል፦ በአገር ጉብኝት ስም በ1830 ዓ.ም. የመጣውና በትግራይ ይንቀሳቀስ የነበረው ጀርመናዊው ፕሮቴስታንት አገር ጎብኚ ሺምፐር (Schimper)፣ የፕሮትስታንት ሚስዮንን በመሐልና በደቡብ ኢትዮጵያ በማስፋፋት የሚታወቀው ሳሙኤል ጐባት (Samuel Gobat) ዋና ዋዎቹ ናቸው። 7.6. የጣልያን ወረራ ፋሺስት ኢጣልያ ኢትዮጵያን ክፋፍሎ ለመግዛት ባደረገው ተደጋጋሚ ዘመቻ ሀገሪቱንና ሕዝቡን አንድ አድርጋ የያዝችውን የኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋሕዶ ቤተክርስቲያንን ማፈራረስና ክርስቲያኖችን መፍጀት ዋነኛው የጦር ዘዴው ነበር። በዚህም አሰቃቂ ወረራና ጭፍጨፋ የሮማ ካቶሊካዊት ቤተክርስቲያን ምዕመናን፣ ካርዲናሎች (ጳጳሳት) እና ፓፓው ለሙሶሎኒ ጦር ከፍተኛ የሆነ የገንዘብ ዕርዳታ አድርገዋል። በተጨማሪም ሰማዕቱና ሐዋርያው ቅዱስ ጴጥሮስ ስለክርስቶስና ስለ ክርስትና የቁልቁሊት ተዘቅዝቆ በተሰቀለባት የሮም አደባባይ በመላው ዓለም ሕዝብ ፊት ኢትዮጵያውያን ክርስቲያኖችን በግፍ የሚጨፈጭፍበትን የሙሶሎኒን የወረራ ዘመቻ " የተቅደሰ ዘመቻ” ብለው፤ መድፍና ታንኩን በመስቀላቸው ባርከው ወደ ኢትዮጵያ ማዝመታቸው ታሪክ የማይረሳው ግፍ ነው። የኢጣልያ ጦር ለሁለት ጊዜ ባደርገው ወረራ በብዙ ሺዎች የሚቆጠሩ ክርስቲያኖችን (ካህናት፣ ምዕመናን፣ ሕጻናትን) ደም በግፍ አፍስሷል፣ 2000 አብያተክርስቲያናት፣ ገዳማትንና አድባራትን አውድሟል፣ ብዙ ታሪካዊና ሃይማኖታዊ ቅርሶችን ዘርፎ ወደ ሮም አግዟል። ከዚህም በላይ በአርበኝነት ለሃይማኖታቸውና ለሃገራቸው ክብር ሲሉ ከኢጣልያ ጦር ጋር ፊት ለፊት ተዋግተው የሞቱትን አርበኛ ክርስቲያኖች ሳይጨምር በየአድባራቱና በገዳማቱ ብዙ ባህታውያን፣ መነኮሳትና ካህናት መስዋእት ሆነዋል። ከጳጳሳቱም መካከል ታሪካቸው ለኢትዮጵያ ክርስቲያን መመኪያ የሆነው አቡነ ጴጥሮስ ቀዳማዊ እና አቡነ ሚካኤል ቀዳማዊ ስለ ሀገራቸውና ስለ ሃይማኖታቸው ሲሉ በግፈኛው ፋሺስት ተገድልዋል። ወስብሐት ለእግዚአብሔር!!!
|
|